ሀብታሙ ግርማ ደምሴ

መግቢያ

ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ትዋሰንበት የነበረው ሰሜናዊ ግዛቷ ኤርትራ በ1991 ከተገነጠለች በኋላ ወደብ አልባ ሆናለች፤ በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ 44 ወደብ አልባ አገራት ያሉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ብዙ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ናት፤ በኤርትራ ነፃነት ማግስት ኢትዮጵያን ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ወደብ እንደ ነዳጅና ሌሎች እቃዎች ሁሉ ከአለማቀፍ ገበያ በግዢ የሚገኝ  ሸቀጥ ነው የሚል አቋም ነበረው፤ የኢህአዴግ ሊቀ-መንበርና የአገሪቱ መሪ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ ለዘመናት ተፈጥሯዊ ድንበሬ የምትለውን ቀይ ባሕር በይፋ አጀንዳነቱ አክትሟል አሉ

የኢፌዲሪ መንግስት የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ

ሆኖም የቀይ ባሕር ጥያቄ በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በልሂቃኑ፣ ምሁራን እና በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ በነበሩ ሃይሎች ዘንድ አጀንዳ መሆኑን ቀጥሎ ዛሬ ደርሷል፤ እንዲያውም የኢህአዴግ መንግስት በ2018 ካበቃ በኋላ የወደብ ጉዳይ ዳግም መንግስታዊ አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል፤ በቀይ ባሕር ቀጠና እየታዩ ያሉ ጂኦ-ፖለቲካዊ ለውጦች፣ እንዲሁም የጅቡቲ ወደብ የኢትዮጵያን የሎጀስቲክስ ፍላጎት በብቸኝነት ሊያሟላ አለመቻል ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በቀይ ባሕር ላይ ያላትን ጥያቄ ቀዳማዊ ብሔራዊ አጀንዳ ለማድረጓ ምክንያቶች ናቸው

የአሰብ ወደብ

የአለማቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተባባሪ ነው

የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆን በአገሪቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ ሊኖረው የሚችለውን መዘዝ በመረዳት የተለያዩ የአለማቀፍ አካላት አገሪቱ ወደብ እንድታገኝ በተለያዩ ጊዜያት እገዛ ለማድረግ ሞክረዋል፤ ለምሳሌ ኤርትራ ከጣሊያን ቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትተሳሰር ከወሰነባቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋታል በሚል አመክንዮ ነበር፤ ከደርግ ውድቀት በኋላ ኤርትራ ነጻነቷን ለመቀዳጀት ጫፍ በደረሰችበት ወቅት የአለማቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ አይፈልግም ነበር፤ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ በርካታ ሁነቶችን መጥቀስ ይቻላል

ሄርማን ኮህን

በ1980ዎቹና 90ዎቹ የአሜሪካ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳይ አስፈጻሚ የነበሩት ኸርማን ኮህን ባንድ ወቅት እንዳሉት የኤርትራ መገንጠል የማይቀር እንደሆነ በታየበት በ1990ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት ኢትዮጵያ ወደብ እንዳታጣ መንግስታቸው ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደነበረ ገልጸዋል፤ በወቅቱ የኤርትራ አማጽያንና የኢትዮጵያ ተወካዮች (ህወሃት/ኢህአዴግ) የድንበር ማካለልና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ለመወሰን የአሜሪካ መንግስት ባዘጋጃቸው ስብሰባዎች የህወሃት/ኢህአዴግ ሊቀ መንበር መለስ ዜናዊ የወደብ ጉዳይ አከራካሪ ስላልሆነ አጀንዳ ሆኖ እንዳይቀርብ ጠይቀው እንደነበር፣ ይህም በአሜሪካ መንግስት በኩል ግርምትን የፈጠረ እንደነበር አስታውሰዋል፤ ዶ/ር ያዕቆብ ሃይለ ማርያም ባንድ ቃለ ምልልሳቸው እንዳሉት በኢትዮጵያ በተካሄደው የ1997ቱ (እ.ኢ.አ) አገራዊ ምርጫ ዋዜማ በጀርመን ኤምባሲ በተጠራ ግብዣ በወቅቱ የጀርመን አምባሳደር የነበሩት ሰው ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ብታነሳ አገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ ነግረውኝ ነበር ብለዋል

ዶ/ር ያዕቆብ ሃይለ ማርያም

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ባለመመለሱ በኢትዮጵያና ኤርትራ ባለፉት ሃያ አምስት አመታት የደረሰው ኪሳራ

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ባለመመለሱ ምክንያት በአፍሪካ ቀንድና ቀይ ባሕር ቀጠና ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በርካታ ችግሮች ተከስተዋል፤ በ1998 በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለተደረገው ጦርነት መሰረታዊ ምክንያት ከሆኑት ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቁ አለመፈታት ነበር፤ ከጦርነቱ በኋላ የሁለቱ አገራት መንግስታት የተከተሏቸው አንዱ ሌላውን የማዳከምና በእጅ አዙር የመውጋት ፖሊሲዎች በአገራቱ ሰላም፣ ልማት እና ብልጽግና ላይ እስካሁን ያልሻረ ጥቁር ጠባሳ አሳርፈዋል፤ ለምሳሌ በኤርትራ የነጻነት ትግል ምዕራፍ መገባደዱን ተከትሎ የፈነጠቀው የዴሞክራሲና ሕዝባዊ መንግስት ምስረታ ትልም እንዲጨናገፍ የሆነው ከአሰብ ወደብ ጉዳይ አለመፈታት ጋር በተያያዘ ነው፤ በ1997 የተዘጋጀው የኤርትራ ህገ መንግስት ጸድቆ ወደ ትግበራ ያልገባበት ምክንያት የኤርትራ ሽግግር መንግስት የብሔራዊ ደህንነት አደጋ ገጥሞኛል በማለቱ እንደሆነ ይታወቃል፤ በመሆኑም ኤርትራ እስከዛሬ ድረስ በአስቸካይ ጊዜ አዋጅ በሚመስል አኳኋን ነው የምትመራው

የኢትዮጵያ የባሕርበር ጥያቄ መልስ አለማግኘቱ በኢትዮጵያ ላይ በርካታ መዘዞዝች አስከትሏል፤ ከእነዚህም አንዱ በ1998  ከኤርትራ ጋር ወደ ጦርነት እንድትገባ ማድረጉ ነው፤ ኢትዮጵያ የባሕርበር ማጣቷ የብሔራዊ ደህንነቷ አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል፤ የአሰብ ወደብ መዘጋትን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሎጀስቲክስ ችግር ገጥሟት እንደነበር ይታወቃል፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ ከጎረቤት አገራትን ወደቦች ለመጠቀም በርካታ ጥረቶች ስታደርግ ብትቆይም በተለያዩ ምክንያቶች ሊሳኩ ባለመቻላቸው በጅቡቲ ወደብ ላይ ጥገኛ እንድትሆን አድርጓታል፤ ይህም አገሪቱ ያለአግባብ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለወደብ ኪራይ እንድታወጣ ምክንያት ሆኗል፤ ይህም ሆኖ እንኳ የጅቡቲ ወደብ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ያለውን የኢትዮጵያ የሎጀስቲክስ ፍላጎት ሊያሟላ አልቻለም፤ በመሆኑም የአገሪቱ የኢኮኖሚ ደህንነት አደጋ ላይ ወድቋል

የአሰብ ጉዳይ እልባት አለማግኘቱ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲፈጠር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ አስተዋጽኦ አድርጓል፤ በ1993  በህወሃት/ኢህአዴግ የሚመራው ማዕከላዊ መንግስትን በጽኑ የፈተነው የውስጥ ፖለቲካ ቀወስ አንዱ ምክንያት የአሰብ ጉዳይ ነበር፤ ይህ ሁነት በህወሃት/ኢህአዴግ ታሪክ ከፍተኛ የሚባል የፖለቲካ ንቅዘትን ያስከተለ እንደሆነ ብዙ ተብሎለታል፤ የፖለቲካ ክፍፍሉን ተከትሎ በርካታ ነባር የህወሃት/ኢህአዴግ የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች ከመንግስታዊና የፓርቲ መዋቅር ተሰናብተዋል፤ ችግሩ ስሩን ወደ አገሪቱ የሲቪልና ወታደራዊ ተቋማት ተዛምቶ ተቋማቱ ከህዝባዊ ጥቅም ይልቅ ለፓርቲ ወግነው እንዲሰሩ ያደረገ፣ በኢህአዴግ ውስጥ የአንድ ግለሰብ (የአቶ መለስ ዜናዊ) እና ቡድን የበላይነት ያሰፈነ፣ በአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እንዲጠብና ኦኮኖሚው ለስርዓቱ አገልጋይ በሆኑ አካላት ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ ምክንያት የሆነ፣ በዚህም በኢትዮጵያ ለሁለት አስርት ዓመታት በላይ ለተከሰቱ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅሎች መነሻ ተደርጎ ይቆጠራል

የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ጥያቄ አለመፈታት በአፍሪካ ቀንድና መካከለኛው ምስራቅ አገራት ላይ ያሳደረው ጉዳት

የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ጥያቄ አለመፈታቱ መዘዙ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ቀንድ አገራት ተዛምቷል፤ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ የአሰብ ወደብ በመዘጋቱ ኢትዮጵያ አማራጭ ወደቦችን ፍለጋ ያማተረችው ወደ ሶማሊያ ወደቦች ነበር፤ ይህ የኢትዮጵያ አካሄድ በሶማሊያ ፖለቲከኞች መካከል ከፍተኛ ውግዘት ያስከተለ ነበር፤ ይህ ተቃውሞ አድጎ የሶማሊያ ወጣቶች የአገሪቱን የውሃ አካላት ከውጭ ወራሪዎች ለመጠበቅ በሚል አልሸባብ የሚባለው ታጣቂ ቡድን መሰረቱ፤ ኢትዮጵያ አልሸባብ በብሔራዊ ደህንነቴ ላይ አደጋ የደቀነ ነው በሚል በ2006  ሰራዊቷን ወደ ሶማሊያ አስገብታ ጦርነት ገጥማለች፤ ኤርትራ በበኩሏ ለአልሸባብ የፋይናንስና ወታደራዊ ድጋፍ ታደርግ ነበር፤ በዚህም ኢትዮጵያና ኤርትራ ካለፉት ሃያ ዓመታት በእጅ-አዙር ጦርነት ውስጥ ነበሩ ማለት ይቻላል

በሶማሊያ የአልሸባብ መፈጠርን ተከትሎ በቀይ ባሕርና የህንድ ውቂያኖስ የውሃ አካላት የሚተላለፉ መርከቦች ደህንነት አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ ምክንያት ሆኗል፤ ይህም በአካባቢው የባሕር ላይ ዝርፊያ በመስፋፋቱ ነው፤ በዚህም ምክንያት ከ2000  ጀምሮ በቀይ ባሕርቀጠና በመላው አለም ስጋትን የደቀነ ጂኦ-ፖለቲካዊ ለውጦች ተስተውለዋል፤ እነዚህን ጂኦ-ፖለቲካዊ ለውጦች በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል

የቀይ ባህር ተጎራባች አገራት

የመጀመሪያው የባሕር ደህንነትን ማስጠበቅ በሚል ሰበብ ተፎካካሪ ፍላጎቶች ያላቸው እንደቻይናና አሜሪካ ያሉ ልዕለ-ሃያላን ቀይ ባሕርና አካባቢውን ለመቆጣጠር እሽቅድምድም ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉ ነው፤ እነዚህ አገራት የባሕር ሃይላቸውን በቀይ ባሕር አካባቢ ማስፈር የጀመሩት ከዚህ በኋላ ነው፤ በዚህም በ2001  አሜሪካ የባሕርሃይሏን በጅቡቲ አሰፈረች፤ ቻይና በበኩሏ በ2008  ከአገሯ ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ የባሕር ጦር ሰፈር በጅቡቲ አቋቋመች፤ በጅቡቲ የጦር ሰፈር ያላቸው አሜሪካና ቻይና የቀይ ባሕር ቀጠና የአለማቀፍ ጂኦፖለቲካ ትኩሳት ነጥብ እንዲሆን እያደረጉት ይገኛሉ

በጅቡቲ የባሕር ጦራቸውን ያሰፈሩ አገራት

ሁለተኛው ለውጥ የቀይ ባሕር ቀጠና በኢራንና በሳዑዲ በሚመራው የአረብ  ሊግ አባል አገራት መካከል ፍጥጫ እንዲነግስ ማድረጉ ነው፤ እንደሚታወቀው የኤርትራ መንግስት ለአልሸባብ ያደርግ በነበረው ድጋፍ ምክንያት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ማዕቀብ እንዲጣልባት ከወሰነ በኋላ ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ገጥሞታል፤ ኢራን ደግሞ ይህን የኤርትራ መንግስት የፋይናንስ ችግር ለማስታገስ ፍቃደኛ ሆና ቀረበች፤ በዚህ መነሻነት በ2008  ኢራንና ኤርትራ ስምምነት አደረጉ፤ በስምምነቱ መሰረት ኢራን ለኤርትራ መንግስት የገንዘብና ቴክኒክ እርዳታ ለመለገስና በምትኩ የአሰብ ወደብን የመጠቀም መብት አገኘች፤ ይህም ኢራን በየመን የሁቲ አማጽያንን እንዲሁም  በሊባኖስ  የሄዝቦላ ታጣቂ ቡድንን በሎጀስቲክስ ለመደገፍ አስችሏታል፤ በቀይ ባሕር ቀጠና ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደትሆንም አድርጓል

የኢራን ካርጎ መርከብ በቀይ ባሕር ላይ ትታያለች
(ምንጭ፡ ASHRAF SHAZLY/AFP/Getty Images)

ከኢራን ጋር በሃይማኖታዊና ጂኦ-ኢኮኖሚ ጥቅም በተጻራሪ የቆሙት የአረብ አገራት  በቀይ ባሕር ጉዳይ ላይ ያላቸውን አትኩሮት በመጨመር በአካባቢው አገራት የውስጥ ጉዳይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጣልቃ ገብተው የኢራንን አካሄድ ለማስቆም ከፍተኛ እንቅስቀሴ ማድረግ ጀመሩ፤ ከዚህም አንዱ በሳዑዲና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ መሪነት በየመን ለአምስት ዓመታት ያህል (2015-2019) በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት የአረብ ሊግ አባል አገራት በቀጥታ ተሳታፊ መሆናቸው ዋነኛው ነው፤ በውጤቱም በየመን የማዕከላዊ መንግስቱ እንዲፈርስ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የመናዊያን ደግሞ ለሞት፣ ስደት እና ረሃብ እንዲጋለጡ ሆነዋል

በአፍሪካ ቀንድና ቀይ ባሕር ቀጠና የቅርብ ጊዜ ጂኦ-ፖለቲካዊ ለውጦች የጋረጡት አደጋ

የየመን ጦርነት በ2019 እንዳበቃ ሳዑዲ አረቢያና ሌሎች የቀይ ባሕር አዋሳኝ አረብ ሊግ አባል አገራት ‹የቀይባሕርካውንስል› የሚል አንድ ድርጅት ፈጠሩ፤ ስምንት አገራትን በአባልነት የያዘው ይህ ድርጅት በዓላማው ‹የቀይ ባሕር ቀጠናን ደህንነት በጋራ መጠበቅ› የሚል ነው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስን ያገለለው ይህ አደረጃጀት ከሁለቱ አገራት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፤ በዚህም ምክንያት የቀይ ባሕርና አካባቢውን ደህንነት ከማሻሻል ልቅ ሌላ ራስ ምታት ሆኗል፤ በቅርብ ዓመታት ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በቀይ ባሕር ላይ ያላቸውን ፍላጎትና ተጽዕኖ እንዲጨምር የሚያደርጉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ እርጃዎችን እየወሰዱ የሚገኙት በዚሁ ምክንያት ነው፤ ይህ የአፍሪካ ቀንድና ቀይ ባሕር ቀጠና ጂኦፖለቲካ ይበልጥ እንዲወሳሰብ ያደረገ ነው

የኢህአዴግ ስርዓት በ2018  በብልጽግና ፓርቲ መሪነት በተመሰረተው መንግስት መተካቱን ተከትሎ የኤርትራና ኢትዮጵያ መንግስታት ልዩ ስምምነት ማድረጋቸው ከሁለቱ አገራት ህዝቦች ባለፈ ለአፍሪካ ቀንድ አገራት ህዝቦች በአጠቃላይ ብስራት ይዞ የመጣ ነበር፤ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ መስከረም 7 ቀን 2018  ከቻይናዉ ሲ.ጂ.ቲ.ኤን (CGTN) ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወደ ሰላማዊ መስመር የተመለሰው የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት የወደፊት አቅጣጫ ምን መሆን እንዳለበት ሲገልጹ እንዲህ ነበር፡-

ኢትዮጵያና ኤርትራ ለረጅም ዓመታት ጥሩ ግንኙነት አልነበረንም፤ አሁን ወደ ሰላማዊ ግንኙነት ተመልሰናል፤ (ግጭት ውስጥ ለመቆየታችን) ተጨባጭ ምክንያት ማቅረብ እንኳ አይቻልም፤ ከአሁን በኋላ ባለፉት ሃያ ዓመታት ያባከንናቸውን እድሎች (የሰላም ሁኔታውን) በፍጥነት በመጠቀም ማካካስ አለብን፤ለሁለታችንም አገራት የጋራ ተጠቃሚነት በፍጥነት ወደጋራ ልማትና ተጠቃሚነት መግባት አለብን

ነገር ግን ብዙ ተስፋ የተጣለበት የሁለቱ አገራት መልካም ግንኙነት ሊዘልቅ አልቻለም፤ የሁለቱ ዓመታት የትግራይ ጦርነት (2020-2022) ያስቆመውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ተከትሎ የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ቅራኔ ውስጥ ገባ፤ ሁለቱ አገራት ዳግም ወደ አለመግባባት ለመግባታቸው ሌላው ምክንያት ከአሰብ ወደብ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፤ በቅርቡ የኢትዮጵያ መከላከያ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመስሪያ ቤታቸውን አመታዊ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ‹የኤርትራ መንግስት የአሰብን ወደብ ኢትዮጵያን እንደፈለገ ለመጠምዘዝ ሊጠቀምበት ይፈልጋል› ብለው ነበር፤ በአጠቃላይ ከሃያ ዓመታት በሃላ የአሰብና ምጽዋ ወደቦችን ለኢትዮጵያ አገልግሎት እንዲሰጡ የተያዘው ውጥን በድጋሚ ህልም ሆኖ የቀረ ይመስላል

በ2023  መገባደጃ ገደማ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በይፋ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ባለድርሻ መሆን እንደምትፈልግ ገለጹ፤ የፈረንጆቹ 2024 አዲስ አመት ዕለት ከራስ-ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ለ50 አመት የሚቆይ የባሕር መውጫ ለማግኘት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ከወቅቱ የሶማሊላንድ ፕሬዚዳት ሙሴ ቢሂ ጋር በአዲስ አበባ ተፈራረሙ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የሶማሊላንዱ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ በወደብ ጉዳይ የመግባቢያ ሰነድ ሲፈራረሙ፤ ጃንዋሪ 1 ቀን 2024 ፣ አዲስ አበባ

ይህን ተከትሎ ሶማሊላንድን የሉዓላዊ ግዛት አካሏ አድርጋ የምትቆጥረው ሶማሊያ ከፍተኛ ተቃውሞ አደረገች፤ የሶማሊያ መንግስት የማያቋርጥ ዲፕሎማሲያዊ ትግል በማድረግ ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ አለማቀፋዊ ጫና እንዲበረታ ሆነ፤ ጎረቤት አገር ኤርትራም ኢትዮጵያ ያነሳችውን የቀይ ባሕር ባለቤትነት ጥያቄ እርሷንም መንካቱ የማይቀር መሆኑን ተረድታ ከግብጽና ሶማሊያ ጋር ሁሉን አቀፍ ጥምረት ለመፍጠር መንቀሳቀስ ጀመረች፤ ሶስቱ አገራት በተደጋጋሚ በመገናኘት ወታደራዊ ትስስራቸው ለማጠንከር ሰሩ፤ ግብጽ በቀጥታ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ መላክ የምትችልበትን አግባብ ከአገሪቱ መንግስት ጋር ተፈራርማ በፍጥነት ሰራዊቷን በሶማሊያ አሰፈረች

ከሶማሊያና ኢትዮጵያ መንግስታት ጋር መልካም ግንኙነት ያላት ቱርክ ሁለቱን አገራት ለማሸማገል እንቅስቃሴ ጀምራ በ2024  መገባደጃ ላይ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አደረገች፤ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ 2025 የመጀመሪያዎቹ ወራት ገደማ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከሶማሊያ (ሶማሊላንድ) ወደ አሰብ መሸጋገሩን የሚጠቁም ንግግር በፓርላማ ንግግራቸው አሰሙ፤ ከዚህ በኋላ የአሰብ ጉዳይ በይፋ ትኩረትን መሳብ ጀመረ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የአሰብ ወደብን የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ለማድረግ ሃይል እጠቀማለሁ ብሎ በይፋ ባይናገርም ጠቅላይ ሚኒስትሩና ከፍተኛ ሹማምንቶቻቸው በተለያዩ ሚዲያዎች እያደረጉ ያሉት ንግግሮች አሰብን በጦርነት የመያዝ ፍላጎት ፍንጭ የሰጠ እንደሆነ በርካታ የፖለቲካና ወታደራዊ ተንታኞች ገልጸዋል

የቱርኪዬው ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሙሃሙድን በማሸማገል በአንካራ ከተማ የሰላምና ትብብር ስምምነት ሲያፈራርሙ

ባለፉት ጥቂት ወራት በርካታ አለማቀፍ ሚዲያዎች ኤርትራና ኢትዮጵያ በድንበሮቻቸው አቅጣጫ ከፍተኛ የጦርነት ዝግጅት እያደረጉ እንዳሉ የሳተላይት ምስሎችን በማስረጃ እያስደገፉ ዘገባ ሰሩ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በ2025 ሚያዚያ ወር የመጀመሪያው ሳምንት ባደረገው የብሔራዊ ደህንነት ስብሰባ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ባለድርሻ የመሆን ጥያቄዋ  (የአሰብ ወደብ ጥያቄዋ) እስካሁን  በነበረው ግለት እንዲቀጥል መመሪያ አስቀመጠ፤ ከዚህ መመሪያ በኋላ የኢትዮጵያ የሲቪልና ወታደራዊ ባለስልጣናት የአሰብ ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት እንደሚሆን በተለያዩ መድረኮች ላይ በግልጽ ሲናገሩ እየተሰማ ነው፤ ለአብነት ለመጥቀስ ያህል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰኔ 4 ቀን 2025 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን በቅርቡ በእጇ እንደምታስገባ ያመላከተ ነው

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመላው የአፍሪካ ቀንድ አገራት ጉዳይ መሆን አለበት!

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ባለመፈታቱ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ከኢትዮጵያና ኤርትራ አልፎ በቀይ ባሕር ቀጠና፣ የአፍሪካ ቀንድና መካከለኛው ምስራቅ አካባቢዎች፣ እንዲሁም በአለማቀፍ ደህንነት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ ችግሩ ዛሬም ድረስ ባለመቀረፉ የቀይ ባሕር ቀጠና የበርካታ አገራት የጂኦፖለቲካ ትኩረት ማዕከል እንዲሆን በማድረግ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ቀንድ አገራት ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ ያደረገ ነው፤ በመሆኑም ይህን ጉዳይ መፍታቱ በኢትዮጵያና ኤርትራ ዘላቂ ጥቅምና የጋራ ብልጽግና መሰረት የሚጥል ከመሆኑም ባሻገር ለአፍሪካ ቀንድና አካባቢው ዘላቂ ሰላም እጅግ ብዙ ፋይዳ አለው፤ ስለሆነም የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄን መመለስ ለአፍሪካ ቀንድ አገራት ሰላምና ልማት ዋስትና ነው፤ በመሆኑም ጉዳዩ የኢትዮጵያ ብቻ ተደርጎ መቆጠር የለበትም፤ ችግሩን በሰላማዊ አግባብ ለመፍታት መላው የአፍሪካ ቀንድ አገራት፣ እንዲሁም የአለማቀፉ ማህበረሰብ ርብርብ ሊያደርግ ይገባል

የዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ በኬንያ ናይሮቢ ከተማ በሚገኘው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ሪሰርች ኮንሶርቲየም (AERC) የምርምር ፌሎው ነው፤በተጨማሪም በናይጀሪያው አንጋፋ የትምህርት ተቋም በሆነው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢባዳን  የፒ.ኤች.ዲ (በኢነርጂ ኢኮኖሚክስ) ተመራማሪ ነው፤ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ አስራ ሁለት መጽሐፍትን የጻፈ ሲሆን፤ በቅርቡ ደግሞ ‹የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ›እንዲሁም ‹የአሰብ ጉዳይና የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት›የተሰኙ ሁለት መጽሐፍትንአሳትል፤ ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው ruhe215@gmail.com  ማግኘት ይቻላል

Leave a comment

Trending