ሀብታሙ ግርማ ደምሴ
እንደመግቢያ
የዚህ መጣጥፍ ርዕስ አድርጌ የወሰድኩት ሐረግ በተውሶ ያገኘሁት መሆኑን ለአንባቢ ማስታወስ እወዳለሁ፤ በአንድ ወቅት ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ አክራሪ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነትን ለመንቀፍ በጻፈው መጣጥፍ የተጠቀመው ‹ኢትዮጵያን ያቀፍናት መስሎን እንዳናንቃት› ሀረግ ነው፤ እንደማስታውሰው የታምራት ነገራ ጽሑፍ ጭብጥ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ህጸጾችን ለማረም ያለመ ነው፤ ‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር ከዘውጌ ብሔርተኞች (Ethno-centric Elites) ብቻ አይደለም የሚመነጨው፣ የኢትዮጵያ ብሔርተኞችም (Ethiopian Nationalists) ብዙ ችግሮች አሉባቸው› በሚለው ላይ እኔም እስማማለሁ
በግሌ የዘውጌ ብሔርተኞችም ሆነ የኢትዮጵያ ብሔርተኞች በአገራችን አንድነት ላይ የጋረጡብንን ችግሮች ለማስታገስ ያስችላሉ ብዬ ከማምንባቸው ተግባራት አንዱ ሰፊው ሕዝብ ባለንበት ዘመን የሚስተዋሉ ቁልፍ ፖለቲካዊና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በመረጃ የተመላ፣ በእውቀት የታገዘ እና በምክንያታዊነት የበለጸገ አቋምና አመለካከት መያዝ አለበት የሚል ነው፤ ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጽንሰ ሃሳብ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ አንካር ጉዳዮች ማለትም ብሔርተኝነትና የብሔር ፖለቲካ፣ ህገ-መንግሥት፣ አገረ-መንግሥት፣ ብሔረ-መንግሥት፣ የብሔር ፌዴራሊዝም፣ የዜግነት ፖለቲካ ወዘተ… ዙሪያ ያለን ግንዛቤ በእውቀት እና እውነት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ጠንካራ አገር ለመገንባት ቁልፍ ሚና ይጫወታል የሚል የጸና እምነት አለኝ
በዚህ መጣጥፍ ‹ሰፊው ሕዝብ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን እንዴት መረዳት አለበት?› በሚለው ነጥብ ላይ የራሴን አተያይ እገልጻለሁ

ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ያለን ግንዛቤ ምን መሆን አለበት?
ኢትዮጵያዊያን አገራችንን እንደምንወድ በተገኘው አጋጣሚ እንገልጻለን፤ ነገር ግን በተግባር አገርን መውደድ ምን እንደሆነ የግንዛቤ እጥረት እንዳለ የሚስተዋል ችግር ነው፤ ለመሆኑ አገር ማለት ምን ማለት ነው? አገርን መውደድ እንዴት ይገለጣል? በዚህ የመጽሐፉ ንዑስ-ክፍል ስለ አገር የሚኖርን እሳቤ በእውቀት (በመርህ) ይሆን ዘንድ እሳቤያዊ-ማዕቀፍ (Conceptual Framework) ለማበጀት ተሞክሯል፤ በዚህም አገር የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ምንነት በአጭሩ ቀርቧል፤ በተጨማሪም አገሬን እወዳለሁ የሚል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እውነተኛ ወዳጅነቱ የሚለካባቸው አግባቦች ተመላክተዋል
ኢትዮጵያን መውደድ እንዴት ይገለጣል?
በእኔ ግንዛቤ አንድ ሰው አንድን ነገር ይወደዋል ብሎ ለመገንዘብ እንደመስፈርት መሆን ያለባቸው ሶስት ተያያዥ ነገሮች አሉ፡- አንደኛው ስለሚወደው ነገር ግንዛቤ ለማግኘት (ለማወቅ) በሚያጠፋው ጊዜ፣ ጉልበት ወይም ኢነርጂ ነው፤ ሁለተኛው የሚወደውን ነገር የግሉ ለማድረግ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት (የጊዜ፣ ጉልበት ወይም ኢነርጂ) ለመክፈል ቁርጠኝነት ነው፤ ሶስተኛ የሚወደውን ነገር ካገኘ በኋላ የእርሱ አድርጎ ለማቆየት በሚያጠፋው ጊዜ፣ ጉልበት ወይም ኢነርጂ (emotion) መሆን አለበት
እንግዲህ መውደድ የምንለው ስነ-ልቦናዊ እንደመሆኑ በቁጥር ለመለካት ከባድ ነው፤ የመውደዱ ነገር በሁኔታዎች ውስጥ ሊለዋወጥ ይችላል፤ እዚህ ጋር የቦታ፣ የጊዜ እና ሌሎች ሁኔታዎች ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል
እውነተኛ ወዳጅ ከሚወደው ጋር ባለው ቁርኝት መርሁ ‹ፍቅር እስከ መቃብር › እንጂ ‹ከራስ በላይ ንፋስ› አይደለም፤ ደስታው ሁሉ በሚወደው ነገር ውስጥ ስለሆነ (የሚወደውን ነገር) ማጣት አይፈልግም፤ ከዚያ ይልቅ አቅሙ የሚችለውን ሁሉ አድርጎ የራሱ አድርጎ ለማቆየት ይጥራል፡፡ ወዳጅ ስለሚወደው ነገር አብዝቶ ጊዜውን እና መንፈሱን ስለሚሰጥ በሚወደው ነገር ላይ አጠቃላይ አካሏዊም ሆነ ስነ-ልቦናዊ ውቅር ላይ አጠቃላይ ግንዛቤ አለው፤ በመሆኑም የሚወደውን ነገር ህልውና (በአዎንታም ሆነ በአሉታዊ) የሚጎዱ ነገሮችን ለመረዳት ይጥራል፤ ያውቃልም፡፡ ስለሆነም ወዳጅ የሚወደውን ነገር ማጣት ስለማይፈልግ የኋለኛውን ህልውና የሚጎዱ ማንኛውንም ተግባራት ሊፈጽም ይቅርና ሌሎች እንኳን (በማወቅም ሆነ ባለማወቅ) ሊጎዱት ቢሞክሩ ዘብ (ጋሻ) ሆኖ በመቆም ከጥቃት ይጠብቀዋል
በአጠቃላይ አገሬን እወዳለሁ የሚል አገሩን ስለመውደዱ የሚገልጽ ከቃላት (ከዘፈን) ባለፈ ተጨባጭ ነገር ሲተገብር መታየት አለበት፤ አገርን ማወቅ ሲባል ቢያንስ የሚከተሉትን ሶስት ጉዳዮችን ለማወቅና ለመመርመር መጣር ማለት ነው፡፡ አንደኛው አገር የምንለው ጽንሰ ሃሳብ ምን ማለት እንደሆነ፣ በዚህም ኢትዮጵያን እንደ አገር መረዳት፤ ሁለተኛው አገር ሃብት መሆኑን መገንዘብ፤ ሶስተኛው የአገርን (የኢትዮጵያን)የስነ-መንግስታዊ ታሪክን በአግባቡ በመረዳት አገሪቱን ለማስቀጠል የሚያስፈልገውን መረዳት እና/ወይም ዋጋ መክፈል መቻል ነው

I. አገር የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ መርመር
አገር የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ህዝቦች የጋራ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅና የሚጋጩ ፍላጎቶቻቸውን ለማስጠበቅ በአንድ መንግሥት ስር ለመተዳደር የሚገቡት ቃልኪዳን ነው፤ በመሆኑም አገር በሚለው ጽንሰ ሃሳብ ውስጥ ህዝቦች (ዜጎች)፣ መንገስት፣ የተለያዩ ተፎካካሪ እና/ወይም የሚጋሩት ፍላጎቶች ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች፣ እነዚሁ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደ አንድ አገር ሕዝብ ሆነው በጋራ ለመተዳደር መነሻ ወይም መሰረት የሚሆናቸው የጋራ ጉዳይ፤ ይህን የጋራ ጉዳይ የሆነውን በአንድነት የመኖር አጀንዳ ሊያሳኩበት የሚችሉበት መንገድ (ሂደት)፤ እንዲሁም እነዚህ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በአንድነት ለመኖር እንዲችሉ በጋራ የሚስማሙበት የጥቅም እና ግዴታ የውል ስምምነት ሰነድ ናቸው
ስለሆነም አገር በሚለው ጽንሰ ሃሳብ ውስጥ አገረ-መንግሥት፣ ህገ-መንግሥት፣ የፖለቲካ ልሂቃን እና ብሔረ-መንግሥት የሚባሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ በመሆኑም አገር ስለሚባለው ነገር የሚኖረን ዕውቀት እነዚህን ጉዳዮች ማወቅ ነው
በአንድ አገር የሚኖሩ የተለያዩ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ፖለቲካዊ ልዩነቶቻቸውን በጎን አድርገው፣ ነገር ግን የጋራ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ተግባራትን የሚከውን አካል አገረ-መንግሥት ይባላል፤ አገረ-መንግስቱ ይህን የህዝቦች የጋራ ጥቅም የማስጠበቅ ኋላፊነቱ በዝቅተኛ ደረጃ ሊከውን የሚገባው ተግባር ሲሆን፣ ዋነኛ ተግባሩ ብሔረ መንግሥት ለመመስረት ለሚደረጉ ሂደቶች መሰረት የሆኑ ተግባራትን ማካሄድ ነው፤ ይህም የተራራቁ የፖለቲካ ፍላጎቶችን ለማቀራረብ የሚስችሉ ህገ-መንግስታዊ፣ ተቋማዊ እና አስተዳደራዊ መሰረተ-ልማቶችን (Soft infrastructures) መገንባት ነው

በመሆኑም የአገረ-መንግሥት አስፈላጊነት የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ወደፊት በጋራ አብረው መኖራቸው ጥቅም እንዳለው ማሳየት፣ የአብሮነታቸው ዋስትና እንዲኖር መሰረት የሚሆነውን የጋራ ኑሮ መመስረቻ የውል ሂደትን ማስተባበር፤ በጋራ የተስማሙበትን የቃልኪዳን ሰነድ ውሎች ሳሸራረፉ እዲከበሩ የማድረግ ሃላፊነት ያለበት ህዝባዊ መንግሥት እንዲቋቋም ማድረግ ነው
የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎችን ጥቅሞች ወክለው በመደራደር በጋራ ሊያድሩበት የሚችሉበት መንግስታዊ ስርዓት የሚዋቀርበትን አግባብ የሚበይኑበት፣ በአንድነት ለሚመሰርቱት መንግሥት ርዕይ የሚቀመጥበት ሂደት ህገ-መንግሥት የማጽደቅ ሂደት ይባላል፡፡ ይህን የጋራ ተጠቃሚነት ይረጋገጥ ዘንድ የተለያዩ የህብረተሰብ አካላትን ጥቅሞች ወክለው የሚከራክሩ/የሚደራደሩ ግለሰቦች/ቡድኖች አሉ፤ እነዚህም የፖለቲካ ልሂቃኖች የምንላቸው ናቸው፤ ህዝቦች በጋራ ለመተዳደር የሚገቡበት የቃልኪዳን ሰነድ ህገ-መንግሥት ይባላል፤ ህገ-መንግሥት የተለያዩ የማህበረሰብ/ሕዝብ ክፍሎች በጋራ ፖለቲካዊ ፍላጎታቸው ላይ የተስማሙበት የቃል-ኪዳን ሰነድ በመሆኑ ለብሔረ-መንግሥት ምስረታው ስኬት ትልቅ እርምጃ ተደርጎ ይወሰዳል
ነገር ግን ህገ-መንግሥት ስለጸደቀ ብቻ ብሔረ-መንግስቱ እውን ይሆናል ማለት አይደለም፤ የብሔረ-መንግስቱ እውን መሆን የሚወሰነው ህገ-መንግስቱን ለማክበር እና ለማስከበር በሚኖረው ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ነው፡፡ ህገ-መንግስቱን ያጸደቁት የፖለቲካ ሃይሎች የመሰረቱት መንግሥት የህገ-መንግስቱን እሴቶች በማክበርና በማስከበር፣ በዜጎች አዕምሮ ውስጥ የአገርን ምስል ማኖር አለበት፤ አገር ማለት ህዝቡና መሬቱ ብቻ ሳይሆን ህዝባዊ (የጋራ) ስነ-ልቦና መፍጠር ሲቻል ነው፡፡ በመሆኑም አገር ማለት እያንዳንዱ ዜጋ በኑሮው (በህይወቱ) ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ ዋስትና የሚሆነው ስርዓት ማለት ነው፤ የአንድ አገር ዜጎች (በባህል፣ በቋንቋ ፣ በእምነት እና በአስተሳሰብ ከሚጋሩትም ሆነ ከማይጋሩት ከሌሎች የአገሩ ዜጎች ጋር) በስነ-ልቦና የተዛመዱ ናቸው፤ ለአንድ አገር ዜጎች የአንዳቸው ችግር ለሌላኛቸውም ህመም ነው፤ የአንዳቸው ደስታ ቢያንስ ለሌሎቹ ሃዘን (ባያስደስት እንኳን) አይሆንም
በህብረተሰባችን ውስጥ ስለ አገር ጽንሰ ሃሳብ ያለው ግንዛቤ የተንሸዋረረ እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ አስረጂዎችን መጥቀስ ይቻላል፤ ለተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ኢትዮጵያ እርስቱ፣ ከአምላክ ተሰጠች ዘለዓለማዊ ስጦታ ስትሆን፤ ለአንዳንዱ ህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢ ናት፤ አገርን ከመንግስታት እና ከመሪዎች ያለመለየት ችግርም እንዲሁ ይስተዋላል፤ ነገር ግን በመንግሥት(ታት) እና/ወይም በመሪ(ዎች) እንጂ በአገር ላይ ቂም አይያዝም የሚለውን የስነ-መንግሥት መርህ የሚጥስ አመለካከት እና/ወይም ተግባራት በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ተመልክተናል (እየተመለከትንም ነው)፤ በመንግስታት/መሪዎች ላይ ተስፋ መቁረጥ ያለ ቢሆንም፣ በአገር ግን ተስፋ መቁረጥ አይገባም፤ በመሆኑም ኢትዮጵያዊነትን በመገንባት ሂደት አንዱ ተግባር መሆን ያለበት ትውልዱን ስለ አገር ጽንሰ ሃሳብ ማስተማር ነው
በኢትዮጵያ ውስጥ የአገር ጽንሰ-ሃሳብን ባለመረዳት ምክንያት የተወለዱ በርካታ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ እንዲሁም የደህንነት ጋሬጣዎች ሲከሰቱ ኖረዋል፤ ዛሬም ይህ ችግር አለ፤ መላ ካልተበጀለት በቀር ለነገው ትውልድ ችግሩ ተባዝቶ መተላለፉ አይቀሬ ነው
ኢትዮጵያን እንደ አገር ካለመገንዘብ ከሚመነጩ አንዱ ህዝቦች ለበርካታ ዘመናት በአንድ አገረ-መንግሥት ስር መቆየታቸውን ዛሬም ሆነ ነገ እንደ አንድ ሕዝብ በጋራ ለመኖር ዋስትና አድርጎ መገንዘብ ነው፤ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የአገረ-መንግስቱ ዋና ተግባር የሚሆነው ብሔረ መንግሥት ለመመስረት የሚስፈልጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው እንጂ በራሱ ግብ አይደለም፡፡ በመሆኑም በጋራ መንግሥት ስር ለበርካታ ዓመታት መተዳደር መቻል ብቻውን እውነተኛ አገር ስለምንለው ጽንሰ ሃሳብ ሙሉ ምስል አይሰጠንም
ህዝቦች የቱንም ያህል በአንድ መንግሥት ስር ቢቆዩ የሚያስተዳድራቸው ስርዓት ቀደም ሲል የተገለጹትን የአገረ-መንግሥት ተግባራትን ካልፈጸመ ገዢያቸው እንጂ መንግስታቸው ሊሆን አይችልም፤ በገዢዎች ስርዓት ውስጥ ህዝባዊ አንድነትን ለማስፈን አይቻልም፤ በመሆኑም ህዝቦች የሚተዳደሩበት ስርዓት.መልክ/ባህሪ ስለአገራቸው የሚኖራቸውን ፍቅር/ክብር ይወስናል፤ ስርዓቱ እንደመንግሥት ሳይሆን እንደ ገዢ ከሆነ ዜጎች የአገር ፍቅር እና ክብር አይኖራቸውም፤ በተቃራኒው ፍትሃዊ ስርዓት ካለ ዜጎች አገራቸውን የሚወዱ እና/ወይም ለአገራቸው ህልውና መስዋዕትነት ለመክፈል የማይሳሱ ይሆናል ፡፡ በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የረጅም ዘመናት የጋራ አገረ-መንግሥትነት ታሪክ ያላቸው ህዝቦች በጋራ እሴቶቻቸው ላይ ተመስርተው ብሔረ-መንግሥት ለመመስረት ካልጣሩ ከመነጣጠል አደጋ ሊርቁ፣ አገራቸውንም ከመፍረስ ስጋት ሊታደጉ አይችሉም
አገር የሚለውን ጽንሰ-ሃሳብ ባለመገንዘብ ከሚፈጠሩ መደናገሮች መካከል ሌላው በባህል፣ ቋንቋ ወይም እምነት መለያየት አገር ለመመስረት እንቅፋት አድርጎ መውሰድ ነው፤ በመሆኑም ተፈጥሯዊ የሕዝብ ልዩነቶችን ጨፍልቆ አዲስ ማንነት በመፍጠር አንድ አገር መገንባት የሚለው አስተሳሰብ ነው፤ ትናነንት ኢትዮጵያን የመሰረቱት አባቶቻችን አንድ ባህል፣ አንድ ቋንቋ ፣ አንድ ሃይማኖት በሚል መርህ ብዝህነትን የሚጎዱ ተግባራት በመከወናቸው፣ የብሔር ጭቆና ትርክት የፖለቲካ ዋናው መታገያ መንገድ ተወስዶ ዛሬ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን አለ

ሌላው አገር የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ በወጉ ካለመገንዘብ የሚመነጭ የአመለካከት ችግር የአንድ አገር ጥንካሬ መሰረቱ ህዝባዊ አንድነቱ መሆኑን በሚገባ ለመረዳት አለመቻል (አለመሞከር)ነው፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የስነ-ልቦና መቀራረብ ወይም መራራቅ በአገራዊ አንድነት ላይ ስለሚኖረው ትልቅ ፋይዳ በተራው ዜጋም ይሁን በአገር መሪዎች ዘንድ እምብዛም ትኩረት ተነፍጎት ኖራል፤ ነገር ግን የህዝባዊ አንድነቱ መሰረቱ ደግሞ ዜጎች እርስ በርሳቸው ያላቸው የስነ ልቦና ቁርኝት ነው፤ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር የሚኖራት ጥንካሬ አንዳችን ሌላኛችንን ለመረዳት በሚኖረን ዝግጁነት ነው፤ የሌሎችን ጉዳት የራሳችንም ጉዳት ባደረግንበት ልክ ነው፤ የአንዱ ቁስል ለሌላውም ህመም መሆን ሲችል ነው፤ የኢትዮጵዊነት ልቡ የአንዳችን ችግር ሌላችንም ችግር ሆኖ መሰማቱ ነው፤ ኢትዮጵያን መውደድ ማለት እርስ በርሳችን መዋደዳችን ነው
አገር የሚለውን ጽንሰ-ሃሳብ በአግባቡ ካለመረዳት ከሚስተዋሉ አመለካከቶች መካከል ህዝባችን የቀድሞና የአሁኑ ስርዓተ-መንግስታትን እና/ወይም መሪዎቹን የሚመዝንበት አግባብ ወይም መስፈርት ነው፤ መንግስታትን (መሪዎችን) የምንመዝንበት አግባብ በአብዛኛው በዘፈቀደ ነው፤ ለምሳሌ በአሁኑ ትውልድ እንደምናስተውለው የመመዘኛ መስፈርት በአመዛኙ የመንግስታቱ/መሪዎቹ ውክልና ለብሔራችን ወይም እምነታችን ካላቸው ቅርበት ወይም ርቀት ነው፤ ይህ ባለፉት ስርዓታት እና መሪዎቻችን ላይ ያለን ዘፈቀዳዊ አረዳድ በማህበረሰባችን ውስጥ ሕዝብን ክሕዝብ በመከፋፈል አገራዊ አንድነታችንን እንዲላላ ምክንያት ነው
ነገር ግን የኢትዮጵያ ስርዓተ-መንግስታት/መሪዎች መመዘን ያለባቸው ስርዓቶቹ አገረ-ብሔር ለመመስረት ከሄዱበት ርቀት ነው፤ የመንግስታቱ ባህሪ ዲሞክራሲዊ፣ አምባገነን ወዘተ…አይነት ባህሪ ቢኖረውም እነዚህ መመዘኛ መስፈርቶች ስርዓቶቹ ብሔረ-መንግሥት ለመመስረት ከሄዱበት ርቀት አንጻር ሚዛን ውስጥ አይገቡም፤ ምክንያቱም መንግስታዊ ስርዓቱ ኢኮኖሚን ቢያሳድግ፣ ትምህርትን ቢያስፋፋ፣ መሰረተ-ልማት ቢያስፋፋ፣ ወዘተ…. የህዝቡን በዘለቄታ በአንድነት የሚኖርበት የፖለቲካ መደላድል የሆኑትን ህገ-መንግስታዊ፣ ተቋማዊ እና አስተዳደራዊ ስርዓት ካልዘረጋ ሌሎች መልካም ስራዎቹ ሁሉ ዋጋቸው እምብዛም ነው
በመሆኑም ስርዓተ-መንግስታት (መሪዎች) መመዘን ያለባቸው ዋነኛ መስፈርት ህዝቡ በአንድነት ይኖር ዘንድ መሰረት የሆኑትን የጋራ የቃልኪዳን ሰነድ ለማዘጋጀት የሄዱበት ርቀት፣ እንዲሁም የፖለቲካ ስርዓቱን ስብራቶች ለመጠገንና የፖለቲካ መረጋጋት ይሰፍን ዘንድ ህዝቡ በፍትሃዊነት በአብሮነት እንዲኖር የሰሩት ስራ ነው፤ ትናንትም ሆነ ዛሬ እንዲሁም ነገ የፖለቲካ ስልጣን የያዘ ስርዓተ-መንገስት መገምገም ካለበት ይህን ተግባር ለመከወን በነበረው፣ ባለው ወይም በሚኖረው ቁርጠኝነት እና ተጨባጭ እንቅስቃሴዎች ነው
II. አገር ሃብት መሆኑን መገንዘብ
አገሩን የሚወድ አገሩን የራሱ ለማደርግ መጣር አለበት፤ የጥረቱ መገለጫም አገሩ የእርሱ እንድትሆን መክፈል የሚገባውን ነገር ለማድረግ ባለው ቁርጠኝነት እንዲሁም አበርክቶት ነው፤ አገሩን የእርሱ እንድትሆን ዋጋ የከፈለ በመሆኑ አገሩን እንደሃብቱ ይቆጥራል፤ ሃብቱ መንፈሳዊ እና/ወይም ቁሳዊ መልክ አለው፡፡ ነግዶ ማትረፍ በአገር ነው፤ ሰርቶ ማደር በአገር ነው፤ አንገትን ቀና አድርጎ መሄድ በአገር ነው፤ ጸቡም ፍቅሩም የሚያምረው በአገር መሬት ነው
አገር ሃብት መሆኑን ለማወቅ በፈረሰ አገር ውስጥ ኖሮ ልዩነቱን ማየት አይጠይቅም፤ ወይም ባዕድ አገር ሄዶ የመገለልና የመድሎ ገፈት መቅመስን አይጠይቅም፤ ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለውና ማመዛዘን የሚችል አገሩ የህልውናው ጉዳይ እንደሆነች መገንዘብ አይሳነውም
ኢትዮጵያ እንደ አገር ለዘመናት ያላቋረጠ የባዕዳንን ሴራ ተቋቁማ ዛሬ እኛ እጅ የደረሰችው እልፍ ትውልዶች በከፈሉት ደምና አጥንት መሆኑን ለሁላችንም የተደበቀ እውነት ወይም እውቀት አይደለም፤ አገሩን እንዲሁ በዋዛ ሳይሆን በመስዋዕትነት የተገኘች በመሆኗ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማወቅ አለበት፤ ይህ ከሆነ ሁሉም ዜጋ አገሩ ሃብቱ እንደሆነች ስለሚገነዘብ እንዲሁ በዋዛ በፈዛዛ ማጣት አይፈልግም፤ እርሱም ለልጆቹ አገሩን ያገኘው ሰርቶ፣ ለፍቶ እንጂ እንዲሁ በነጻ እንዳልሆነ ስለሚያስገነዝባቸው ልጆቹም አገራቸውን፣ ሃብታቸውን እንዲሁ ለልጆቻቸው የሚያወርሱበት ስንቅ ይኖራቸዋል፤ አገር የምትቀጥለው በዚህ መንገድ ነው እንጂ ምንም እንዲሁ እጃችን አጣጥፈን የእግዚአብሔር ቃልኪዳን ያላት መለኮታዊ ባህሪ በመስጠት አይደለም
አገር ሃብት እንደመሆኑ በአግባቡ ካልተጠበቀ ሊወድም እንደሚችል፣ በአግባቡ ከያዝነው ግን ሃብቱ እያደገ እንደሚሄድ መረዳት አለብን፤ በመሆኑም ከአባቶቻችን የተረከብነው አገር (ሃብት) የማያልቅ ጥሪት አድርገን መውሰድ የለብንም፤ በዚህም የማያልቅ ጥሪት አድርገን በዝብዘን ወደ ጥፋት (ወድመት) እንዳይንመራው ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤ ጥንቃቄ ካላደረግን አገር ከእጃችን ልትወጣ እንደምትችል በአጽንኦት ልንገነዘብ ይገባል፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አባቶቹ ነጻነቷን አስጠብቀው ያወረሱትን እርሱም እሴት ጨምሮበት ለልጆቹ የማውረስ የሞራል ግዴታ አለበት
III. አገርን መውደድ አገርን ለማስቀጠል በሚከፈል መስዋእትነት ይገለጻል
አገርን መውደድ አገርን ለማስቀጠል በሚከፈል መስዋእትነት ይለካል፤ እንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አገሩን መውደዱ የሚለካው አገሪቱ ውስጥ ያሉ ብዝሃ ባህል፣ ቋንቋ ፣ ታሪክ፣ እምነት እና የፖለቲካ እሳቤዎችን አክብሮ ማስከበር የሚያስችል ተክለ ስብዕና በመገንባት ነው፤ አገር የሚገነባው በአንድ ወጥ ባህል፣ ቋንቋ ወይም የፖለቲካ እሳቤ ሳይሆን በስብጥር ህብሮች መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገናል፤ በዚህም ከእሳቤያችን፣ ባህላችን፣ ቋንቋችን፣ ሃይማኖታችን የተለየ ወንድሞቻችን/እህቶቻችን.እናቶቻች/ አባቶቻችን ክብር ሊኖረን ይገባል፤ይህ ለእነርሱ ክብር ብለን ብቻ የምናደርገው ሳይሆን የራሳችንን የስብዕና መሰረቶች ለማስከበር ነው፤ እምነታችንን፣ ባህላችንን፣ ቋንቋችንን እና ፖለቲካ እሳቤዎቻችን ሌሎች እነዲከብሩልን እኛ ቀድመን እነርሱን ማክበር አለብን፤ እንዲህ ሲሆን አብሮነታችን ይጎለብታል፤ እኔ ብቻ ልድመቅ፣ የእኔ ብቻ ፊት ይቅደም፣ የሌሎቹ አያገባኝም የሚሉ እሳቤዎች በመሰረቱ አብሮ የሚያናኑር ሳይሆን የሚያቃቅር ነው

ዛሬ የአገራችን ሉዓላዊነት በውጭ ሃይሎች የመደፈር ሙከራ እየተደረገበት ያለው በልሂቃኖቻችን መካከል ይህ መሰረታዊ ስብዕና በእጅጉን በመሸርሸሩ ነው፤ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ታሪክ ሆና የምትቀረው የፖለቲካ ሽኩቻው ክልሂቃን አልፎ ህዝባዊ መሰረት ሲይዝ ነው፤ እስካሁን የአገርን አንድነት አስጠብቆ ያቆየው በህዝቡ (በማህበረሰቡ) ውስጥ ያልጠፋው በጎ ስብዕናዊ መሰረት ነው፤ በዚህ ረገድ እስከ 90 በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ አማኝ መሆኑና የሃይማኖት አስተምህሮቶች የህዝቡን የሞራል እና ስነ-ምግባር መሰረቶችን በማነጽ ረገድ ፋይዳቸው ጉልህ በመሆኑ ነው፤ ነገር ግን ይህ ህዝባዊ (ማህበረሰባዊ) የስብዕና ጥሪት ከጊዜ ወደ ጌዜ እየተሸረሸረ በመሄድ ላይ ይገኛል
ህዝቡ በልሂቃኑ መካከል እንዳለው የመናናቅና የጠላትነት መንፈስ ከያዘ ያን ጊዜ አገር ፈረሰ ማለት ነው፤ ነገር ግን የፖለቲካችን መገለጫ የሆነው የልሂቃን የስብዕና ስሪቶች (መጠላለፍ፣ ቂም፣ በቀል እና/ወይም የተበዳይነት ስነ-ልቦና) ከፖለቲካ ልሂቃን ጎራ ወጥቶ ህዝባዊ (ማህበረሰባዊ) የስብዕና መሰረት ሊይዝ ባለመቻሉ አገር እንደ አገር ሊቆይ ችሏል፤ ይህ ህዝባዊ (ማህበረሰባዊ) መልካም ስብዕና የፖለቲካ ልሂቃኖቻችን መገለጫ በሆነው በጎ ያልሆነ ስብዕና እንዳይዋጥ፣ በዚህም የአገር እና ሕዝብ ህልውና እንዳያበቃለት መከፈል የሚገባው ማንኛውም መስዋዕትነት ሊከፈል ይገባል፤ በእውነተኛነት አገሩን የሚወድ እንዲህ ያለውን መስዋእትነት ለመክፈል አይሳሳም፤ አገርን በተግባር መውደድ የሚገለጸው በእንደዚህ አይነቱ በጎ ተግባር ነው
አገር በምንለው ጽንሰ ሃሳብ ውስጥ ሕዝብ እና ልሂቃን አሉ፡፡ ሕዝብ የግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ ድምር ነው፡፡ ሕዝብ የአገር መሰረት ነው፡፡ ጠንካራ ህዝባዊ እሴት ጠንካራ አገር እና መንግሥት ለመፍጠር መሰረት ነው፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ያለን ህዝቦች ለአገር ያለን ስሜት አንድ አይነት ሊሆን አይችልም፤ አንዳንዱ አገሩን አጥብቆ የሚወድ ሊሆን ይችላል፤ መርሁም ኢትዮጵያ ትቅደም (Ethiopia First) ሊሆን ይችላል፤ ለአንዳንዶች ደግሞ ብሔረሰባቸው ሊበልጥባቸው ይችላል፤ ይህ አይነት የተከፋፈለ የሕዝብ የፖለቲካ አመለካከት የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ በዓለም በርካታ አገሮች በአገራቸው የውስጥ ጉዳይ በከፍተኛ ርቀት የተከፋፈሉ ህዝቦች አላቸው፤ የዓለም አገራት (የአውሮፓ እና የአሜሪካ አገራትን ጨምሮ) የውስጥ ፖለቲካን ከመረመርን በበርካቶቹ አገራት ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚሳየን የመገንጠል ዓላማን ያነገቡ (በሰላማዊም ሆነ በትጥቅ ትግል የሚደገፉ) ሃይሎች እንዳሉ ነው
ነገር ግን የአገራቱ የፖለቲካ ስርዓት መሰረት እንዲሁም የየአገራቱ የፖለቲካ ልሂቃን በአብዛኛው ማለት በሚቻል ሁኔታ የክፍፍሎቹን መነሻ ምክንያች ለማጥበብ እና ዜጎችን ለማቀራረብ ሲሰሩ እንጂ ቅራኔዎችን ለማስፋት ሲጥሩ አይስተዋልም፤ ይህን የሚደርጉም በከፍተኛ የአገር ክህደት ወንጀል የሚጠየቁ፣ ለዚህም የፖለቲካ ስርዓቱ ቁርጠኛ ነው፤ ለዚያም ነው ተጠናቆ ያለቀ አገር የለም የሚባለው
በእርግጥም የፌዴራሊዝም እና ስነ-መንግሥት ምሁራን እንደሚገልጹት የብሔረ-መንግሥት ግንባታን የጀመሩ እንጂ የጨረሱ አገራት የሉም፡፡ በመሆኑም በአገሩ ጉዳይ ላይ የተለየ የፖለቲካ አቋም ያለውን ዜጋ አገሩን እንደማይወድ፣ አልፎም እንደከሃዲ ወይም ባንዳ መቁጠር አይገባም፤ ይልቁንም የተሳሳተ ፍረጃ ከመስጠታችን በፊት ለምን እንዲህ አይነት አቋም ሊይዝ እንደቻለ ለመገንዘብ መጣር ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ይህን በአገሩ ላይ ያለውን አመለካከት በበጎ እንዲቀይር ማድረግ የምንችለው እኛው ራሳችን ነን
በእውነቱ ከሆነ ማንም ተጠቃሚ የሆነባትን አገር ሊጠላ አይችልም፤ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ታሪካቸው በተሟላ ሁኔታ እና በአግባቡ ያልተጻፈ ህዝቦች ስለአገራቸው አንድ አይነት ስሜት ይኖራቸዋል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፤ አንዳንዱ የኢትዮጵ ታሪክ አይወክለኝም የሚል ይኖራል፤ አንዳንዱ ደግሞ ያለፈው ስርዓት የሃይማኖት ጭቆና አድርሶብኛል ብሎ በሃገሩ ሙሉ እምነት እና ፍቅር ላይኖረው ይችላል፤ ይህ አዲስ ነገር ሊሆንብን አይገባም፤ በእርግጥ የቅራኔ ታሪክን ብቻ እያነሱ ሕዝብን ለመከፋፈል ማዋል ተገቢ አይደለም፤ ነገር ግን የቅራኔ ታሪክ መካድ ወይም ማሳነስ ይበልጥ አገራዊ አንድነታችንን ይጎዳዋል
ስለሆነም ባለፈው የአብሮነት ታሪካችን ያጎደለባቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ ማወቅ ይጠበቅብናል፤ ታዲያ እነዚህን ኢትዮጵያዊያን ባንዳ ወይም ከሃዲ ከማለት ተቆጥበን፣ ይልቁንስ ቁስላቸውን በፍቅር ለመሻር መትጋት አለብን፤ ቁስላቸውን የምንሽረው በዋናነት ስሜታቸውን ለመረዳት በመሞከር ነው፤ ለወዳጃችን ምሬቱን፣ ስቃዩን፣ ብሶቱን የመረዳትን ያህል ስጦታ የለም፤ ኢትዮጵዊን አገራችንን የመውደዳችን መገለጫ፣ ለአገራችን ያለንን ፍቅር የምንገልጽበት ውዱ ስጦታችን አንዳችን ሌላችንን ቁስል፣ ህመም ለመረዳት በምናሳው ዝግጁነት ነው፤ አገርን መውደድ ከዚህ በላይሊገለጽ አይችልም
እንግዲህ እንዲህ ያለው በሳል ስብዕና እንደ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣ የአገር ሕዝብ በጋራ ስንኖር ለሚኖሩን ግንኙነቶች የተግባቦት ጤናማነት መሰረት በመሆኑ ግንኙነቶቻችንን ሁሉ ሰላማዊ በማድረግ ጠንካራ አገርና ሕዝብ ለመመስረት ዋስትና ይሆናል ፤ በመሆኑም አገርን መውደድ ማለት እርስ በርስ ተዋደን መኖር ማለት እንደሆነ መገንዘብ አለብን፤ ኢትዮጵያን እንወዳለን የምንል ሁሉ እንደግለሰብ የሚኖረን መልካም ስብእና ለምንወዳት አገራችን ሰላም፣ እድገት እና ህዝባዊ አንድነት መሰረት በመሆኑ መልካም እሴቶችን ማዳበር አለብን
የአዘጋጁ ማስታወሻ:- የዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ በኬንያ ናይሮቢ ከተማ በሚገኘው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ሪሰርች ኮንሶርቲየም (AERC) የምርምር ፌሎው ነው፤ በተጨማሪም በናይጀሪያው አንጋፋ የትምህርት ተቋም በሆነው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢባዳን የሶስተኛ አመት የፒ.ኤች.ዲ (በኢነርጂ ኢኮኖሚክስ) ተመራማሪ ነው፤ በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ አስር መጽሐፍትን የጻፈ ሲሆን፤ በቅርቡ ደግሞ ‹የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ› እንዲሁም ‹የአሰብ ጉዳይና የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት› የተሰኙ ሁለት መጽሐፍትን አሳትሟል፤ ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው ruhe215@gmail.com ማግኘት ይቻላል





Leave a comment