ሀብታሙ ግርማ ደምሴ
መግቢያ
ኢትዮጵያ ኤርትራ ነጻነቷን እስካገኘችበት እስከ 1991 ዓ.ም ድረስ 97 በመቶ የሚሆነው የወጪና ገቢ ንግዷን ታከናውን የነበረው በአሰብ ወደብ በኩል ነው፤ ከኤርትራ ነጻነት በኋላ ወደብ አልባ የሆነቸው ኢትዮጵያ አሰብን በኪራይ ስትጠቀም ቆይታለች፤ ነገር ግን የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በ1998 ዓ.ም መቀስቀሱን ተከትሎ የአሰብ ወደብ ተዘጋ፤ በዚህም ምክንያት የአገሪቱ ብሔራዊ አደጋ ላይ ወደቀ

በወቅቱ ኢትዮጵያ የነበራት አማራጭ የጅቡቲ ወደብን መጠቀም ነበር፤ ነገር ግን የጅቡቲ ወደብ የኢትዮጵያን አንድ አራተኛ ብቻ የሚሆነውን የወደብ ፍላጎት ማስተናገድ የሚያስችል አቅም የነበረው መሆኑ በኢትዮጵያ ትልቅ የሎጀስቲክስ፣ ብሎም የብሔራዊ ደህንነት ችግር አጋጥማል፤ ከፈረንጆቹ ሚሊኒየም መባቻ በኋላ ባሉት ዓመታት የኢትዮጵያን ፍላጎት መሰረት በማድረግ የጅቡቲ ወደብ ማስፋፊያ ተደረገለት፤ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ከ90 እስከ 97 በመቶ የሚሆነውን ንግድ የምታከናውነው በጅቡቲ ወደብ ነው

ጂኦ-ኢኮኖሚክስ ምንድነው?
ጂኦ-ኢኮኖሚክስ አንድ አገር ጆኦግራፊያዊ አቀማመጧ የኢኮኖሚ ደህንነቷን፣ ብሎም ብሔራዊ ደህንነቷን አደጋ ላይ እንዳይውደቅ ጂኦ-ፖለቲካዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ የምታደርገው እንቅስቃሴ ማለት ነው፤ ጂኦ-ኢኮኖሚክስ ከመደበኛው የኢኮኖሚክስ አስተምህሮ (በዓላማው የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ወጪ ቆጣቢ በሆነ ሁኔታ ለመድረስ የውስን ሃብት አመዳደብ ቀመር የሚያስቀምጥ) የሚለየው ዓላማው አንዲት አገር ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ ጂኦግራፊያዊ ሁኔታዎችን በመጠቀም የኢኮኖሚ እና/ወይም ጂኦፖለቲካዊ ፍላጎቶቿን ማሳካት እንድትችል ማድረግ መሆኑ ነው

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከጂኦ-ኢኮኖሚክስ አንጻር በሁለት መልኩ ይታያል፤ በአንድ በኩል አገሪቱ የወደብ አልባ በመሆኗ ለመሰረታዊ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች አስፈላጊ የሆኑት የፍጆታ እና/ወይም የማምረቻ ግብአቶችን ከአለማቀፍ ገበያ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ሆነ የአገሪቱን ምርቶችን ለአለማቀፍ ገበያ ለማድረስ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያጋጠማት መሆኑ ነው፤ በሌላ በኩል የባሕር በር ያላቸው ጎረቤት አገራት ወደብን እንደመሣሪያ ተጠቅመው በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ያላቸው ፍላጎቶችና ተጨባጭ ተግባራት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ከሆነችበት ካለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ጀምሮ የተስተዋለ ችግር መሆኑ ነው
ጥናቶች እንደሚያሳዩት የወደብ አገልግሎት የተሳለጠ መሆን ለኢኮኖሚ እድገት እንዲፋጠን ከማድረግ አንጻር ያለው ፋይዳ በሶስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፤ የመጀመሪያው ወደብ አንድ አገር በአለማቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነቷን ከፍ በማድረግ ንግድ ለኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦው እንዲጨምር ስለሚያደርግ ነው፤ ወደብ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ወሳኝ የሚሆንበት ሁለተኛው አግባብ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር፣ መሰረተ-ልማት እንዲሁም ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ በማድረግ ባለው ወሳኝ ሚና ነው፤ በሶስተኛ ደረጃ የምናየው የወደብ አስፈላጊነት የማሪታይም ዘርፍ ለኢኮኖሚ እድገት ባለው አስተዋጽኦ ነው
ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗ የአለማቀፍ ንግድ ተወዳዳሪነቷን ቀንሶታል
ወደብ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ መሰረታዊ ነው፤ በተለይ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር እና እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ላላቸው እንደኢትዮጵያ ላሉ አገራት ወደብ የደም ስር ያህል አስፈላጊ ነው፤ ወደብ ያላቸው አገራት ወደብ ከሌላቸው አገሮች ሲነጻጸሩ አለማቀፍ ንግድን በቀጥታ፣ በፍጥነት፣ በቅልጥፍና እና አነስተኛ ወጪ መገበያየት ይችላሉ፤ በአንጻሩ ወደብ የሌላቸው አገራት ለአለማቀፍ ንግድ መስመር የሌሎች ወደብ ያላቸው ጎረቤቶቻቸው ላይ ጥገኛ ይሆናሉ፤ የወደብ ተደራሽነትና የኢኮኖሚ እድገት እጅግ የተሳሰሩ ጉዳዮች ናቸው
የወደብ ተደራሽነት የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ወጪን በመቀነስ አንድ አገር ከአለማቀፍ ገበያ ጋር ያላትን ትስስር ያሳድጋል፤ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገራት ወደብ ከአገራት ጋር የሚኖርን የሁለትዮሽ ንግድ ግንኙነት ደረጃ የሚወስ ነው፤ ኩሊባሊ እና ፎንታኝ ‹South-South trade› በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጥናታቸው እንደተመለከተው ወደብ አልባ የአፍሪካ አገራት የወደብ ተደራሽነታቸው በ10 በመቶ እንዲጨምር ቢደረግ አመታዊ የውጪ ንግድ አፈጻጸማቸው በአማካይ በሃያ በመቶ ያድጋል
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ወደብ አልባ የአፍሪካ አገራት በሚገጥማቸው የሎጀስቲክስ ችግር ምክንያት የወጪና ገቢ ሸቀጦች ዋጋ ከፍተኛ ያደርገዋል፤ የዓለም ባንክ በ2014 ያደረገው አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ወደብ የሌላቸው ወደብ ካላቸው የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸሩ በአለማቀፍ ንግድ የሎጀስቲክስ ወጪያቸው በሶስት እጥፍ ይጨምራል፤ የወደብ ችግር ያለባቸው አገራት ወደብ ከሚያገኙበት አገር የጉምሩክ ስነ ስርዓት ለማለፍ በሚገጥማቸው መዘግየት ምክንያት የወጪ ንግዳቸው ላይ ተጽዕኖ ይደርሳል፤ ጃንኮቭ እና ፍሩንድ የተባሉ ተመራማሪዎች ‹Trading on time› በሚል ርዕስ ያሳተሙት ጥናት ውጤት እንደሚገልጸው ወደብ አልባ አገራት ምርቶች ከጉምሩክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በሚገጥማቸው ችግሮች ምክንያት በሚኖር የንግድ መጋተት በየእለቱ የወጪ ምርቷቸው በአንድ በመቶ እንዲቀንስ ያደርገዋል

የዓለም ባንክ ጥናት ውጤት እንደሚያሳየው ወደብ አልባ የሆነቸውና 95 በመቶ የሚሆነው የአለማቀፍ ንግዷን በጅቡቲ ወደብ በኩል ያደረገችው ኢትዮጵያ በጅቡቲ መንግስት በየጊዜው የሚቀያየረው የጉምሩክ ስነ ስርዓት በሚፈጥረው ቢሮክራሲያዊ ችግር አስመጪዎችና ላኪዎች ለተለያዩ ተጨማሪ ወጪዎች ይዳረጋሉ፤ ይህ የሎጀስቲክስ መጉላላት ጭነቶችን በወቅቱ ወደ መርከብ ለመጫንም ሆነ ከወደብ አንስቶ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት አስቸጋሪ ስለሚያደርግ አገሪቱን ለተጨማሪ የትራንስፖርት፣ የመጋዘን ኪራይ እንዲሁም ተያያዥ ወጪዎች ዳርጓል፤ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በየአመቱ ከ1.5 እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ወጪ ታወጣለች
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ድርጅት (UNIDO) በ2017 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ጥናታዊ ሪፖርት ውጤት መሰረት በኢትዮጵያ ከወደብ ችግር ጋር ተያይዞ የወጪ ምርቶችን አጓጉዞ ወደ ሸማቾች ለማድረስ የሚወስደውን ጊዜ በሳምንታት ያህል እንዲዘገይ ያደርጋል፤ በተለይ እንደ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ቡና፣ ወዘተ… ያሉ በቀላሉ የሚበላሹ የግብርና ምርቶችን በሰዓቱ ለገበያ ማድረስ ስለማይቻል በወጪ ንግድ አፈጻጸም ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳዳረ ያለ ችግር ነው፤ የአለማቀፍ የቡና ድርጅት (ICO) እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ (NBE) ያደረጓቸው ጥናቶች እንዳመላከቱት በኢንዱስትሪ ፓርኮች በጨርቃጨርቅ ምርቶች ላይ የተሰማሩ አምራቾች ምርቶቻቸው ለአለማቀፍ ገበያ በታዘዙበት ጊዜ ሰሌዳ ማቅረብ ባለመቻላቸው ለተለያዩ ቅጣቶች (በዋናነት የዋጋ ቅናሽ እንዲያደርጉ) ተዳርዋል፤ በዚህም በኢትዮጵያ በወጪ ንግድ የተሰማሩ ላኪዎችና አምራቾች በአብዛኛው ጊዜ እስከ 20 ቀናት በሚደርሰው መዘግየት ምክንያት በሚደርስባቸው የዋጋ ቅናሽ በአማካይ ከ20-25 በመቶ የሚሆን የወጪ ንግድ ገቢያቸውን ያጣሉ
ብሩኪንግ ኢንስቲትዩሽን (Brookings Institution) የተባለ ተቋም በ2021 ያደረገው ጥናት ውጤት እንደሚጠቁመው ኢትዮጵያ በወደብ የሎጀስቲክስ መዘግየት ምክንያት በ2021 ዓ.ም ከቡና ወጪ ንግድ ማግኘት የሚገባት የውጭ ምንዛሬ በ18 በመቶ እንዲቀንስ ሆኗል፤ የአሜሪካው ተራድኦና ልማት ድርጅት (USAID) በ2018 ባካሄደው ጥናት ላይ እንደተመለከተው በኢትዮጵያ የቡና ላኪዎች ለትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አማካይ ወጪ ከቡና ሽያጭ ከሚያገኙት ገቢ 28 በመቶ ይደርሳል፤ በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ቡና በአለማቀፍ ገበያ ዋጋው ከፍ እንዲል በማድረግ ተወዳዳሪነቱን እንዲቀንስ እያደረገ ያለ ችግር ነው
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን (EIC) እና ማኪንሲ( McKinsey & Co) የተባለው አለማቀፍ አማካሪ ድርጅት በ2020 ዓ.ም በጋራ ያካሄዱት ጥናት ውጤት እንደሚያሳየው በጨርቃጨርቅ ምርት ላይ የተሰማሩ አምራቾች በወደብ ችግር ምክንያት ምርቶቻቸውን በወቅቱ ለአለማቀፍ ገበያ ማቅረብ ስለሚቸግራቸው ከደንበኞቻቸው የሚደርስባቸውን አመኔታና ቅጣት ለመቀነስ የአየር ትራንስፖርት ወይም የአውሮፕላን ካርጎ ለመጠቀም ይገደዳሉ፤ የአውርፕላን ካርጎ ከመርከብ ትራንስፖርት አንጻር ዋጋው በአራት እጥፍ የሚጨምር በመሆኑ ገቢያቸውንና ትርፋማነታቸውን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ
አድርጓል
ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ ወደ አገር ውስጥ በምታስገባቸው ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር አድርጓል፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የንግድና ልማት ማዕከል (UNCTAD) በ2020 ዓ.ም ባወጣው የጥናት ሪፖርት እንደተጠቀሰው ኢትዮጵያ የወደብ ተደራሽነት ችግር ምክንያት የትራንስፖትና ሎጀስቲክስ ወጪ ከገቢ ሸቀጦች ዋጋ ከ40 እስከ 50 በመቶ እንዲሆን ያደረገ ነው፤
በጥናቱ እንደተገለጸው በአንጻሩ ወደብ ያላቸው የአፍሪካ አገራት የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ወጪ ከገቢ ምርቶች ዋጋ ከ10 እስከ 20 በመቶ ብቻ ነው
በወደብ ችግር ምክንያት በሚገጥም የትራንስፖትና ሎጀስቲክስ ችግር የሚደርስ የኢኮኖሚ ኪሳራ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ በርካታ ምሁራን እንደ አለማቀፍ ምሳሌ የሚጠቅሱት የጅቡቲ ወደብ ኮሪደርን ወይም ኢትዮጵያን ነው፤ ኢትዮጵያ የወደብ ችግሩ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች፤ ከእነዚህም መካከል በጅቡቲ ወደብ ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ አማራጭ ወደቦችን መፈለግ አንዱ ነው፤ ሌላው ደግሞ የአገሪቱ የአለማቀፍ ንግድ ኮሪደር የሆነው የኢትዮ-ጅቡቲ መስመር የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ መሰረተ ልማቶች የማሸሻል ስራ አንዱ ነው፤ ከእነዚህ ተጠቃሹ በ2010 ዓ.ም የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አቅም የማሳደግና ፕሮጀክት ነው
ከቻይና መንግስት በተገኘ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር የተከናወነው ይህ ፕሮጀክት ቀድሞ የነበረውን የባቡር መሰረተ ልማት በከፍተኛ ደረጃ በመቀየር 752 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የኤሌክትሪክ ሃይል የተገጠመለት የባቡር ሃዲድ ግንባታ በ2016 ዓ.ም ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፤ በውጤቱም የወጪና ገቢ ሸቀጥ ጭነቶችን ከመሃል አገር ወደ ጅቡቲ ወደብ ለማድርስ እና/ወይም ለማስገባት ይፈጅ የነበረው ጊዜ በአማካይ ከ72 ሰዓታት ወደ 12 ሰዓት፣ እንዲሁም የሎጀስቲክስ ወጪን በአማካይ ከ20 እስከ 30 በመቶ እንዲቀንስ አስችላል፤ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ፕሮጀክት የሎጀስቲክስ ስርዓቱ ቀልጣፋ እንዲሆን በማድረጉ አመታዊ ጥቅል ምርት ላይ የ0.5 በመቶ ጭማሪ እንዲያሳይ አስተዋጽኦ አድርጓል

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የንግድና ልማት ማዕከል (UNCTAD) በ2020 ዓ.ም ‹Review of Maritime Transport › በሚል ርዕስ ይፋ ያደረገው ጥናት እንደጠቆመው እንደኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ እና ዛምቢያ ያሉ ወደብ አልባ አገራት ከወደብ ጋር ተያይዞ የሚገጥማቸው ችግር ቢፈታ ኢኮኖሚያቸው በአማካይ በሁለት በመቶ እንዲያድርግ ያደርጋል
ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲቀንስ አድርጓል
ሮድርጌ፣ ኖቴቡም እና ፓሊስ የተባሉ ተመራማሪዎች በ2020 ያሳተሙት የጥናት ውጤት እንደሚጠቁመው የወደብ አገልግሎት ከንግድ ጋር ተያይዞ ያሉ ሌሎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች፣ ለምሳሌ የሎጀስቲክስ፣ የማኑፋክቸሪንግ እና የአገልግሎት ዘርፎች እንዲጠናከሩ ያደርጋል፤ የወደብ ከተሞች የኢንዱስትሪ መንደሮች መናኸሪያ ናቸው፤ ምክንያቱም በወደብ አቅራቢያ መሆናቸው ጥሬ እቃዎችን ከውጭ ለማስገባት እና/ወይም ምርቶችን ወደ ዉጭ ገበያ ለመላክ የሚያስፈልገውን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ስሚቀንስ፣ በዚህም ምርትን አምርቶ ወደ ገበያ ለማቅረብ ወጪን ስለሚቀንስ ነው፤ በዚህም አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸው በአለማቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ስለሚሆን በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲያድግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል

‹The Cost of Being Landlocked› በሚል ርዕስ አርዪስ፣ ራባላንድ እና ማርቲዩ የተባሉ ተመራማሪዎች በ2010 ዓ.ም ባሳተሙት የጥናት ስራቸው እንደተመለከተው ወደብ አልባ አገራት የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ወጪቸው ከፍተኛ በመሆኑ፣ በዚህም የማምረቻ ወጪያቸው ከፍ ስለሚል ሸቀጦቻቸው በአለማቀፍ ገበያ ውድ ይሆናሉ፤ ሊሞ እና ቪነብልስ የተባሉ ተመራማሪዎች በጥናታቸው እንዳረጋገጡት ወደብ አልባ አገራት ወደብ ካላቸው ጋር ሲነጻጸሩ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ወጪያቸው በ50 በመቶ ከፍ ይላል፤ በተጨማሪም ወደብ አልባ አገራት ምርቶቻቸውን አለማቀፍ ሸማቾች (ገዢዎች) በሚፈልጉት ወቅት ለማቅረብ ይቸገራሉ፤ ይህም የንግድ ተወዳዳሪነታቸውን (ተመራጭነታቸውን) በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሰዋል
ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗ ኢኮኖሚዋና ብሔራዊ ደህንነቷ አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጓል
በወደብ ችግር ምክንያት በሚገጥም የትራንስፖትና ሎጀስቲክስ ችግር የሚደርስ የኢኮኖሚ ኪሳራ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ በርካታ ምሁራን እንደ አለማቀፍ ምሳሌ የሚጠቅሱት የጅቡቲ ወደብ ኮሪደርን ወይም ኢትዮጵያን ነው፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የንግድና ልማት ኮንፍራንስ በ2020 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት እንዳሳሰበው ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ ላይ ጥገኛ መሆኗ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ስትራቴጂያዊ ስጋት ውስጥ እንዲወድቅ ያደረገ በመሆኑ ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋል ብሏል፤ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄን የመፍታት ጉዳይ ከኢኮኖሚው አልፎ የአገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት ከአደጋ የመታደግ ፋይዳ ያለው ነው፤ በመሆኑም ሁሉም የአፍሪካ ቀንድ አገራት የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በዚህ አግባብ ተረድተው አገሪቱ በሰላማዊ መንገድ ወደብ የምታገኝበትን መፍትሔዎች ማፈላለግ ለነገ የማይሉት የቤት ስራ ነው
የአዘጋጁ ማስታወሻ:- የዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ በኬንያ ናይሮቢ ከተማ በሚገኘው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ሪሰርች ኮንሶርቲየም (AERC) የምርምር ፌሎው ነው፤ በተጨማሪም በናይጀሪያው አንጋፋ የትምህርት ተቋም በሆነው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢባዳን የሶስተኛ አመት የፒ.ኤች.ዲ (በኢነርጂ ኢኮኖሚክስ) ተመራማሪ ነው፤ በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ አስራ ሁለት መጽሐፍትን የጻፈ ሲሆን፤ በቅርቡ ‹የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ› እንዲሁም ‹የአሰብ ጉዳይና የኢትዮኤርትራ ግንኙነት› የተሰኙ ሁለት መጽሐፍትን አሳትሟል፤ ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው ruhe215@gmail.com ማግኘት ይቻላል





Leave a comment